Skip to main content
x

በየዓመቱ የሚዘጋጀው ሁለተኛው የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዓለም አቀፍ ዓውደ ርዕይ ከዓርብ፣ ሰኔ 22 ቀን 2010 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ለሁለተኛ ጊዜ መካሄድ ጀምሯል፡፡ ከ60 በላይ ኩባንያዎች ተሳትፈዋል፡፡  

      የንግድ ትርዒቱን የከፈቱት የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታዋ ወ/ሮ ሕይወት ሞሲሳ እንደገለጹት፣ ለአገሪቱ ፈጣን ዕድገት መጎልበት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ዘርፉ ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ እንቅስቃሴ አብዛኛውን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚነካ በመሆኑ፣ በርካታ መዋዕለ ነዋይ የሚፈስበትና ከፍተኛ የገንዘብ ዝውውር የሚካሄድበት ዘርፍ ነው፡፡ ስለዚህ ራሱን የቻለ ቋሚ ዓውደ ርዕይ እንዲኖረው ተፈልጎ የተሰናዳ ስለመሆኑ ተገልጿል፡፡

በዚህ ዘርፍ የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ በሰፊው መሰማራቱ ወሳኝ በመሆኑም  ከፖሊሲ ቀረፃ ጀምሮ እስከ ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ድረስ የግሉን ዘርፍ በባለቤትነት እንዲሳተፍ ማድረግ መሠረታዊ የመንግሥት ተግባር ስለመሆኑም ሚኒስትር ዴኤታዋ ተናግረዋል፡፡ የግሉ ዘርፍም የተጣለበትን ኃላፊነትና ሚና በተደራጀና በብቃት በመወጣት ለአገር ብልፅግና አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

የዓውደ ርዕዩ አዘጋጅ የኢትዮ ሐይላንድ ኢቨንት ኦርጋናይዘር ኩባንያ የቦርድ አባል አቶ እስራኤል ተስፋዬ እንዳሉት፣ ለሁለተኛ ጊዜ የተዘጋጀው ዓውደ ዕርይ  በዘርፉ ተዋናዮች መካከል መነቃቃት ለመፍጠርና ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን እንደመሆኑም የአፍሪካ፣ የእስያና የመካከለኛ ምሥራቅ አገሮች እንዲሳተፉ መጋበዛቸው ተገልጾ፣ በርካታ ኩባንያዎችም እንደሚሳተፉ አስታውቀው ነበር፡፡ ይሁንና በኢትዮጵያ በነበረው ፖለቲካዊ አለመረጋጋትና ተያያዥ ምክንያቶች ሳይሳተፉ የቀሩ ቢሆንም፣ በመጪው ዓመት ስብጥሩ የሰፋ የውጭና የአገር ውስጥ ተሳታፊዎች እንደሚገኙበት ያላቸውን ተስፋ አዘጋጆቹ ገልጸዋል፡፡

የአገሪቱ የትራንስፖርትና የሎጂስቲክስ ወጪ በኪሎ ሜትርና በቶን ሲለካ ውድ ስለመሆኑ ተደጋግሞ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ ጥናቶችም ይህንኑ እንደሚጠቁሙ የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ ዘርፉ በአብዛኛው ኋላ ቀር አሠራርን የሚከተልና እሴት በማይጨምሩ ተዋናዮች የተጥለቀለቀ መሆኑ ለወጪው ከፍተኛነት ትልቁን አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ይታመናል ብለዋል፡፡ በመሆኑም መንግሥትና የግሉ ዘርፍ ተቀራርበውና ተረዳድተው ጊዜው በሚጠይቀው ቅልጥፍናና ዘመናዊነት ልክ ዘርፉን በዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ ውጤታማ የሚያደርግ እንቅስቃሴ ማድረግ ግድ እንደሚላቸው አስታውቀዋል፡፡

የጋራ መድረኮችን በማመቻቸትና በመስኩ ላይ ያተኮሩ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ዓውደ ርዕዮችን ማዘጋጀት፣ ለትብብርና አብሮ ለመሥራት የሚረዱ ዋነኞቹ መሣሪያዎች መሆናቸውን ወ/ሮ ሕይወት ተናግረዋል፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዓለም አቀፍ ዓውደ ርዕይ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ትልቅ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡

የተፈጠሩ ወቅታዊ ችግሮች እንደሚቃለሉ በማመን በመጪው ዓመት በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች የሚሳተፉበት ዓውደ ዕርይ ለማሰናዳት ዝግጅቱ ከወዲሁ መጀመሩን የኢትዮ ሐይላንድ ኩባንያ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡ በ2011 ዓ.ም.  የሚዘጋጀው ሦስተኛው ዓውደ ርዕይ በትራንስፖርት፣ በሎጂስቲክና በወደብ አገልግሎት መስክ ኢትዮጵያ ከምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ጋር የፈጠረቻቸውን ትስስሮች ታሳቢ በማድረግ እንደሚሰናዳ አዘጋጆቹ አስታውቀዋል፡፡ የሎጂስቲክና የትራንስፖርት ኩባንያዎችም ሊፈጠሩ ከሚችሉ አዳዲስ ገበያዎችና አሠራሮች ጋር ራሳቸውን እንዲያላምዱ በማገዝ ከኢትዮጵያ ውጭ ከሚገኙና ኩባንያዎች ጋር አሁን ካላቸው የበለጠ ጠንካራ ግንኙነት እንዲፈጥሩ እንደሚረዳቸው ተስፋ ተደርጓል፡፡

ካለፈው ዓርብ ጀምሮ ለሦስት ቀናት ለሕዝብ ክፍት የነበረው ዓውደ ዕርይ ጎብኚዎች በነፃ እንዲታደሙበት የተሰናዳ ሲሆን፣ በትራስፖርትና ሎጂስቲክስ መስክ ያሉ አዳዲስ ቴክሎጂዎች፣ የፈጠራ ሥራዎችና ምርቶችን ጨምሮ የተለያዩ መዝናኛዎችን  ያካተተ ነበር፡፡ ባለፈው ዓመት በተካሄደው ዓውደ ዕርይ ከተሳተፉ ኩባንያዎች መካከል በጎማ ቴክኖሎጂ አዳዲስ ፈጠራዎችን በማስተዋወቅ ጥቅም ላይ የዋለ የተሽከርካሪ ጎማ መልሶ ጥቅም እንዲሰጥ የሚያድረግ ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ ተግባራዊ ስለመደረጉና መሰል ይዘቶች መዘገባችን ይታወሳል፡፡